የፖለቲካ መርሃ-ግብራችን / Our Program

፩. ፩. ራዕይ

የዐማራ ሕዝብ ፀረ-ዐማራ የሆነ ማንኛዉንም ሕዝባዊ ጥቃት በመመከት በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመስራት፣ ሀብትና ንብረት የማፍራት መብቱ ተከብሮ፣ የማንነት ክብሩና ልዕልናው ተረጋግጦ፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቹን ያለ ገደብ ተጠቅሞ እንዲሁም ለደረሰበት የሰብዓዊና የስነ ልቦና ቁስል ተገቢውን ፍትህ አግኝቶ ሲኖር ማየት ነው።

፩. ፪. ተልዕኮ

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት /መዐሕድ/፣ ራዕዩን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ አራት መሰረታዊ ተልዕኮዎችን አንግቦ የተነሳ የዐማራ ሕዝብ ድርጅት ነው። እነዚህም፡-

ሀ. ማንቃት፤

የዐማራ ሕዝብ ታሪካዊ ማንነቱን እንዲያውቅ፣ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶቹን በአግባቡ እንዲለይ፤ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፎችን በመለየት ጠላት በረቀቀ መንገድ የሚያደርስበትንና ያደረሰበትን ጥቃት እንዲመመርመርና እንዲረዳ ማስቻል። የዐማራ ሕዝባዊ አንድነትና ወንድማማችነት እንዲያብብ ሊከወኑ የሚገባቸውን ተግባራት ማስተዋወቅ። የዐማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ገንቢ መስተጋብር እንዲሁም ጠላቶቹን ለይቶ ለማወቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መስራት፡፡ የዐማራን ሕዝብ ማንነትና ኢትዮጵያዊ ዜግነት በተገቢው ሁኔታ ልዩነቱንና አንድነቱን ለይቶ ማስረጽ። የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት/መዐሕድ/ ይህንን ድፍርስ አስተሳሰብ የጠራ እንዲሆን ጠንክሮ ይሰራል፡፡

ለ. ማደራጀት፤

የዐማራ ሕዝብ በረቀቀ መንገድና በጉልህ የሚደርስበትን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና እንዲሁም የዘር ማጽዳት ወይም የዘር ማጥፋት ጥቃቶችን ለማስቆምና ለመከላከል እንዲችል ባግባቡ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ነው። በተጨማሪም በየአካባቢው ከከፍተኛ ሕዝባዊ ብሶትና ጭቆና የተነሳ የሚፈጠሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ባግባቡ በተደራጀና በተቀናጀ አመራር የነጻነት ጊዜን ሊያፋጥን በሚያስችል አደረጃጀት ማዋቀር ያስፈልጋል። መዐሕድ ከዚህ በፊት በየአቅጣጫው በቡድንና በተናጠል ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ጠንካራና የማይንበረከክ አደረጃጀት ማዋቀር። አስፈላጊነቱ ጎልቶ የሚታይ ክፍተት በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለመሙላት መላው የዐማራ ሕዝብ ድርጅት፣ በመላው የዐማራ ሕዝብ ልጆች የተባበረ ክንድ አደረጃጀቱን በየጊዜው በማሳደግ በዐማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውንና ያንዣበበውን አደጋ በመከላከልና በመመከት ለወገን ደራሽነቱን ለማረጋገጥ ጠንክሮ ይሰራል።

ሐ. ማብቃት፤

የዐማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ በሚኖርባቸዉ አካባቢዊ ቦታዎች ሁሉ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ የጎለበተ እንዲሆንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ዉክልና የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንዲችል መዐሕድ ይሰራል። ማህበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ እውቀቱና አመለካከቱ ዳብሮ፤ በኢኮኖሚያዊ ውድድሮች ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችለው አቅም ፈጥሮ፤ እራሱን ከማንኛውም ጥቃት ሊከላከልበት የሚያስችለዉ ትሥሥርና አደረጃጀት ፈጥሮ፤ ከሌሎች ዜጎች ጋር በእኩልነት መርህ የሚኖርባት አገር ባለቤት መሆን እንዲችል አበክሮ መስራት የድርጅታችን መዐሕድ ትኩረት ይሆናል።

መ. መከላከል፤

የዐማራ ሕዝብ ሕልውናውን ለመታደግና በአገሩ እኩል ዜጋ ለመሆን የሚያደርገው ንቅናቄ በጠላቶቻችን ዘንድ በቸልታ እንደማይታይ መዐሕድ ይገነዘባል። በመሆኑም ቀድመው ዓይናቸውን በገለጡና ወገናቸውን ለመታደግ በሞከሩ ጀግኖች ከነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የትግል ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬዋ እለት እየደረሰ ያለው የጠላት ጥቃት ዘመን የማይሽረው መሪር ሀቅ ነው። እስከ ዛሬ ይነሱ የነበሩት የዐማራ ህዝብ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴዎች ባግባቡ ፍሬ ሳያፈሩ የቀሩት ጠላትን አሳንሶ ከማየትና ከሚያደርሰዉ አደጋ ለመከላከል ዝግጁነታችን በቂ ስላልነበር ነዉ። በመሆኑም መዐሕድ እንቅስቃሴዎቹን በከፊል በህቡዕ ከማድረጉ ባሻገር እራሱን የቻለ የጠላትን ጥቃት የሚመክትና ሁለገብ ተግባራዊ ሀይል ማቋቋም አስፈላጊነቱን ያምናል።

 

፩. ፫. ዓላማ

ሀ. በዐማራ ሕዝብ ላይ ዳግም የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል እንዳይከሰት መሥራት። የዐማራ ሕዝብ እራሱን እንዲከላከል ብሎም የመኖር ህልውናውን እንዲያረጋግጥ ማስቻል። በተለይም ላለፉት 26 ዓመታት በዐማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል በጥልቀት መመርመርና ለደረሰውም ጉዳት ተገቢ ሕዝባዊና ዓለማቀፋዊ እዉቅና እንዲያገኝ ማስቻል።

ለ. የዐማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሻው የሥራ መስክ፣ በፈለገው አካባቢ፣ የመኖር   መብቱን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርአት ውስጥ ተገቢውን ውክልና እንዲያገኝና የሚመጥነውን የፖለቲካ ሚና እንዲጫወት ማስቻል።

ሐ. የዐማራ ሕዝብ ከደረሰበት ሁለንተናዊ ጉስቁልና እንዲያገግም የዐማራ ወንድማማችነት በተለይም ፖለቲካዊ፡ ኢኮኖሚያውና ማህበራዊ ህብረቶች እንዲፈጠሩ መስራት።

መ. መዐሕድ በሕዝቦች መካከል በመከባበርና መፈቃቀድ በጋር የመኖር ሂደት ያምናል። የዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ለዐማራ ሕዝብ እንዲዉል መዐሕድ ይሰራል።

 

ሠ. የዐማራን ሕዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲሁም የፍትሕና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲመሰረቱ መስራት። በዐማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችና ጥቃት መረጃዎች ባግባቡ ተሰብስቦና ተጠናቅሮ ታሪኩን ለትዉልድ ማስተላለፍ።

. በፋሽስት ወያኔ ትግሬ ስርዐት የተነጠቁትን የዐማራ ሕዝብ ታሪካዊ መሬቶችን ለማስመለስ መዐሕድ ተግቶ ይሰራል። ዐማራዊ ማንነታቸዉን የተነጠቁ ዐማሮችን ማንነት ማስመለስ።

 

 

. በዐማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል የሚመረምር አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋምና ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ።

ቀ. የዐማራ ሕዝብ ማንነት መገለጫዎች ታሪካችን ቋንቋችንና ባህላችን ለማሳደግና ለመጠበቅ መዐሕድ ይሰራል።

 

፩. ፬. ግብ

ሀ. የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እንዲሁም የመኖር ሕልውናዉ እንዲረጋገጥ፤ በተለይም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ተደራጂቶ በእኩልነትና በብልጽግና እንዲኖር መዐሕድ ይሰራል። የዐማራን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ፖለቲካዊ ድርድር ያደርጋል።

. የጠለሸው የዐማራ ሕዝብ ማንነትና ገጽታ ታድሶ፣ የዐማራ ሕዝብ ታሪካዊ አበርክቶት በክብር እንዲዘከር መዐሕድ ይታገላል።

. የዐማራ ሕዝብ ታሪካዊ የመሬት ግዛቶች፡ የመንግስትነትና ህዝባዊ ታሪኮችና ባህልና ዘፈኑ እንዲጠበቁና እንዲያድጉ ብሎም በጉልህ ደምቀዉ እንዲጻፉና በትምህርት ተቋማት እንዲካተቱ መዐሕድ ይሰራል።

መ. ለዐማራ ሕዝብ የሚበጁ፣ ዘላቂና ስልጡን አሰራርን መሰረት ያደረጉ፣ በሕገና ደንብ የሚመሩ፣ ነፃነት ያላቸው ጠንካራ የዴሞክራሲና ሲቪክ ክድርጂቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፍትህና የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲገነቡ መዐሕድ ይሰራል።

ሠ. በዐማራ ሕዝብ ላይ በደረሰዉ የዘር ማጥፋትና ማፈናቀል ዋነኛ ተዋናኝ የሆኑትን ግለሰቦችና ድርጂቶች ወይም ወንጀለኞች በህግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ መዐሕድ ይታገላል።

ረ. የዐማራ ሕዝብ እውነተኛ ታሪክ ከፈጠራው ተለይቶ እንዲወጣ ማድረግ። ብሎም የዐማራ ሕዝብ ማንነት እንዲከበርና የጠለሸዉ ገጽታ እንዲታደስ በመታገል በዐማራ ህዝብ ላይ የተፈጠረውን ጥላቻ ፈጽሞ እንዲወገድ ማድረግ።

Read in PDF