በከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙት የጎንደር ዐማራ ወገኖቻችን ከመዐሕድ የተሰጠ መግለጫ !!!

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት /መዐሕድ በጎንደር ዐማራ ላይ የተከሰተውን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ትኩረት እንደሚያሻው ያሳስባል፡፡

በጎንደር ዐማራ በህወሃት/ወያኔ ጠንሳሽነትና በቅማንት ኮሚቴ ነን ባዮች አቀጣጣይነት ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና አሁንም በተለያዩ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶች እየተሰቃዩ፣ እየተራቡ እና እየተጨነቁ ለሚገኙ ወገኖቻችን መዐሕድ በድጋሚ የተሰማውን ሐዘን ይገልፃል። ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ ብዙ ሕዝብ በስጋት እና በመፈናቀል የእንቅስቃሴ እና የመሠረታዊ አቅርቦት መናጋት እንዳለ ተገንዝበናል። በዚህም የገበያ እንቅስቃሴ እና የምግብ አቅርቦት ችግር እንዳለ አረጋግጠናል። ችግሩ በአፋጣኝ እንዲፈታ እና የአካባቢው ማህበረሰብም ወደቀድሞው የተረጋጋ ህይወቱ እንዲመለስ የክልሉ መንግስት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው የዐማራ ሕዝብ ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝም መዐሕድ ከተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየሠራ ይገኛል።
ምንም እንኳን የዐማራ እና የቅማንት ህዝብ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተወራርሶ ሲኖረው ተጋርቶ ሲያጣ ደግሞ ተዛዝኖ የኖረ ሕዝብ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለዬ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ለማሳካት የተለያዩ ቡድኖች በሚያካሂዱት ያልተገባ ድርጊት የህዝቡን አብሮነት የሚፈታተኑ ችግሮች ሲስተዋሉ እናያለን። በተለይ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ፣ በማንነት ስም የዐማራውን ሕዝብ ስቃይና መከራ ለማባባስ የተጠና፣ መዋቅራዊና በፖሊሲ የተደገፈ ስትራቴጂን በመጠቀም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተሄደበት ያለውን መንገድ ተገቢ እንዳልሆነ መዐሕድ ያምናል በፅኑ እንደሚታገለውም ያስገነዝባል፡፡ ስለሆነም፡-
1. ሕወሓት/ወያኔ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ከቀድሞው ብአዴን (የአሁኑ አዴፓ) እና ራሳቸውን የቅማንት ማንነት ኮሚቴ ነን ብለው በወከሉ አካላት ፖለቲካዊ አሻጥር እና ውሳኔ ያለ ህዝቡ ምክክር፣ ይሁንታ እና ፈቃድ ወደ ቅማንት የተጠቃለሉ ቀበሌዎች በአዲስ ጉዳያቸው እንዲጣራ ጭምር እንጠይቃለን፡፡
2. ማንኛውም ሰው በሰውነቱ የሚከበርባት ሀገር ትገንባ ዘንድ የተለዬ ፍላጎት ያለው ግለሰብም ይሁን ሕዝብ መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ፤ ይህም ሲባል በባህሉ፣ በማኅበራዊ ስሪቱ እና ባለጉዳዩ ሕዝብ በአግባቡ እና በአጥጋቢ ሁኔታ መክሮ፣ ዘክሮ እና ፈቅዶ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ውጭ ሌሎችን እየበደሉ ወይም እየገፉ መብትን በዘላቂነት ማስከበር አይቻልም። ይህ በየትኛውም ወገን ተቀባይነት የለውም። በተለይ የሀገሪቱ እና የአካባቢው ሁኔታ ባልተረጋጋበት ወቅት ሕዝቡን ወደከፋ ጉዳት፣ መፈናቀል፣ ጭንቀት እና ስጋት መዳረግ ከኃላፊነት የሚመነጭ ነው ብለን አናምንም።
3. መንግስት ይህንን ጉዳይ ከመከሰቱ በፊት በሚገባው መንገድ እና ደረጃ የመፍታት ሥራ እንዳልሠራ፣ ሕዝብን እንዲያገለግሉ በአካባቢው ያስቀመጣቸው የፓለቲካ፣ የፀጥታ እና የመከላከያ አመራሮች ችግሩን ትኩረት ሰጥተው ከማገልገል ይልቅ እንዝላልነታቸው እና አባባሽ ሚናቸውን አምኖ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው እና መፍትሔ እንዲፈለግለት እንጠይቃለን። ከዚህ ጋር በተያያዘም የሚመለከታቸው አካላት ከመንግስት ጎን በመሆን ችግሩ የተወሳሰበ ጉዳት ከመፍጠሩ በፊት እንዲፈታ እንዲረባረቡ፣ በዘላቂነትም መፍትሔ እንዲያገኝ እንዲተባበሩ ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት ጋር በመምከር እና ችግሩን በማረጋጋት ዘላቂ መፍትሔ መሻት እንዳለባቸው እንመክራለን፡፡
4. የመገናኛ ብዙኀን ሚዛናዊ፣ ገለልተኛ እና ወቅታዊ ዘገባዎችን በማቅረብ፤ የአካባቢውን ታሪክ፣ ባህል እና ፍላጎት በትክክል እና በተጠያቂነት የሚያቀርቡ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና መሪዎችን ከሕዝብ ጋር በማገናኘት ወቅታዊ እና አስተማማኝ መረጃ እና ግንዛቤ በማቅረብ ሕዝብ እንዳይወናበድ እና ለሌሎች የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ
5. መጠቀሚያ ከመሆን እንዲከላከሉ እንጠይቃለን፡፡ ከዚህ ባለፈም በችግሩ ምክንያት ለተለያዩ ጉዳቶች እና መፈናቀል የተጋለጡ ወገኖች እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉበትን መረጃ እና መንገድ ለሕዝቡ እና ለመንግስት በኃላፊነት እንዲያቀርቡ፤ ብሎም ጠብ-አጫሪና ወገንተኛ ዘገባዎችና አውታሮችን በመቋቋም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡
6. መንግስት በሕዝቡ መካከል ችግር የፈጠሩ፣ ችግሩን የሚያባብሱ፣ እና መፍትሔውን የሚያደናቅፉ አካላትን በአስቸኳይ በህግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝም መዐሕድ በጥሞና ክትትል ደረጋል፡፡
7. በሕዝቡ ስቃይና ጉዳት ላይ የፓለቲካ ትርፍ ለማገኘት የሚተጉ ድርጅቶች፣ የመገናኛ አውታሮች፣ አክትቪስቶች እና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እናሳስባለን፡፡ መንግስትም እነዚህን ቡድኖች እና ግለሰቦች ተከታትሎ ለህግ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡
8. የአካባቢው የመንግስት አካል፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው የዐማራ ሕዝብ ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ የምግብ፣ የሕክምናና መሠረታዊ አቅርቦቶች የሚሟሉበት ሁኔታ እንዲመቻች መዐሕድ ይጠይቃል፡፡

መዐሕድ በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው በቅማንት ስም የሚነግዱትን ጥቂት የቅማንት ተወካይ ነን ባዮች የእልቂት መልክተኞችንና በገንዘብና በሎጂስቲክ ከበስተኋላ ሆነው ግፊት የሚያረጉትን ሕወሓት / ወያኔን አጥብቆ ይኮንናል:: ቅማንት ቅጥረኞችን ከመካከሉ አስወግዶ ከዐማራ ወገኑ ጋር ሰላሙን አስከብሮ እድገቱን እንዲቀጥል ይጠይቃል::

ድል ለዐማራ ሕዝብ !!!
መዐሕድ
19.11.2018
……… read in pdf ለጎንደር ሰቆቃ የተሰጠ መግለጫ

Share this post