የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለነጻነት !

 

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ)  ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለነጻነት !

በሀገራችን ኢትዮጵያ የጭቆናና ግፍ ምንጭ የሆነው አምባገነናዊ አገዛዝ ከመቸውም ግዜ በከፋ ሁኔታ የሕዝባችንን የሰቆቃ ዘመን አራዝሞታል ። የሰላም አየር ተንፍሶ በሀገሩ በነጻነት የመኖር ተስፋው ተሟጧል ።ይህን አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ እልባት ሰጥቶ በምትኩ በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ መሠረት የሰው ልጅ ስብዕና ተከብሮ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት አዲስ የዲሞክራሲና የሰላም የታሪክ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድና የለውጥ አጋሮቻቸው የቀረበውን ተስፋ ሰጭ ጅማሮ ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የመዐሕድ የልዑካን ቡድን ወደ አገርቤት ይጓዛል።

ወደ ሀገርቤት የሚጓዘው የመዐሕድ የልዑካን ቡድን በመዐሕድ ሰብሳቢ ዶር አፈወርቅ ተሾመ የሚመራው የልዑካን ቡድን ኮሎኔል አለበል አማረ የመዐሕድ የአገር ውስጥ መምሪያ ኃላፊ ፣ ኢንጂነር ታደሰ ሙላት የመዐሕድ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊና አቶ ያለው ይስማው የመዐሕድ ምክር ቤት አባል ያካተተ ነው።

መዐሕድ በግፍ የፈሰሰው የዐማራው ህዝብ ደም፣ የዐማራው ሕዝብ ሰቆቃና ብሶት የፈጠረው ፣ ለዐማራ ሕዝብ ህልውናና ማንነት መረጋገጥ ፣ጠመዝማዛና  እሾሃማውን  የትግል መንገድ እየተጓዘ ዛሬ ላይ የደረሰ ድርጅት ነው። የዐማራ ሕዝብን ጥቃትና ዕልቂት ለማስቆም ፣ ዐማራው ከሀገሩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲገለል የተጣለበትን የዘረኞች ማዕቀብ ለመስበር ፣ ዐማራው የጀመረው የመደራጀት ሂደት ባፋጣኝ ውጤታማ ይሆን ዘንድ መዐሕድ በዐማራ ሕዝብ መካከል በመገኘትና በመመካከር ለዐማራ ሕዝብ አንድነት ይሰራል።

የመዐሕድ ልዑክ የዐማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ይዞታ በሚመለከት እንዲሁም ብሔራዊና  ሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ ከለውጡ የመንግስት ኃይሎች ጋር ይመክራል።

የመዐሕድ ልዑክ ከታሪካዊ የዐማራው ግዛት ውጭ የተለያየ አሰቃቂ ጥቃቶች እየደረሰባቸው ለሚኖሩት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዐማሮች ሁኔታና ዕጣ ፈንታ ከሚመለከታቸው የመንግስት የለውጥ ኃይሎች ጋር ይነጋገራል።

የመዐሕድ ልዑክ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴውን ይገመግማል፣ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር በዐማራ ብሔርተኝነትና ቀጣዩ የትግል ሂደት ዙሪያ ሃሳብ ይለዋወጣል።

የመዐሕድ ልዑክ በሀገር ውስጥ ካሉና ከውጭ ከገቡ የዐማራ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ተቋማት ጋር በዐማራዊ ወንድማማችነት መንፈስ ይመክራል። የመስዋዕትነቱን ክብደት በመቀነስ የድሉን ግዜ ሊያፋጥን የሚችል ዐማራዊ የትግል አንድነት እንዲፈጠር ይጥራል።

የመዐሕድ ልዑክ በባህርዳር ፣ በጎንደር፣ በወልዲያና በደብረ ብርሃን በመገኘት ዓላማ መር ምክክሮችና ውይይቶችን ያካሄዳል።

መዐሕድ ፣ መላው የዐማራ ሕዝብ  የመዐሕድን  ልዑካን ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ ይተባበር ዘንድ  ወገናዊ ጥሪውን በታላቅ አክብሮት ያቀርባል።   read in pdf ….Back to Ethiopia for Freedom

ድል ለዐማራ ሕዝብ !

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

መዐሕድ

 

Share this post