ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ መግለጫ | ባህር ዳር ላይ በግፍ የታሰሩ የአማራ ልጆች በአስቸኳይ ይፈቱ!

መጋቢት 16, 2010 ዓ.ም.
ቁጥር: aapo029/18

ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ መግለጫ

ባህር ዳር ላይ በግፍ የታሰሩ የአማራ ልጆች በአስቸኳይ ይፈቱ!

አማራን ማህበራዊ ደስታ እና ሰላም እንዳይኖረው አደርጋለሁ በማለት ምሎ ተገዝቶ የመጣው እብሪተኛው የወያኔ ትግሬ ፋሽሰት መንግስት በዘወትር አሽከሩ ብዓዴን አማካኝነት በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ሰላማዊ ወጣት የአማራ ምሁራንን ወደ ማጎሪያ ስፍራ ወስዶ በማሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ምሁራን የታፈሱት በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው ለአማራ ህዝብ ነጻነት የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት ህጉ የሚጠይቀውን ሁሉ ሲያሟሉ ቆይተው፤ የቅድመ ምስረታ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ዕቅድ ለመንደፍ ለእራት በተሰባሰቡበት ሰዓት ነው፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ዜጎች እንክብካቤ እንጅ እስራት እና እንግልት አይገባቸውም ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ማንኛውንም ዓይነት የአማራን ህዝብ እንቅሰቃሴ በተመለከቱ ቁጥር አይናቸው ደም የሚለብሰው የስርዓቱ ቁንጮወች ይህ እንዲሆን ፈፅሞ አይፈልጉም፡፡ የአማራ ህዝብ ያለበት ነገር ሁሉ ያንገበግባቸዋል፡፡ ቅናት እና ፍርሃት በእጅጉ ያውኳቸዋል፡፡ ሞት ሞት ይሸታቸዋል፡፡

በተመሳሳይም ከወያኔው ማሰቃያ እስር ቤት በህይወት ተርፈው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን አስመልክቶ የደስታ ጊዜ ለማሳለፍ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በእንድ ጓደኛቸው ቤት የተሰባሰቡ የነጻነት ታጋዮች በግፈኛው ስርዓት ማናለብኝነት እንደገና ለእስራት ተዳርገዋል፡፡ እነዚህም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የአማራ ልጆች ናቸው፡፡

አማራ ከሌሎች ጋር ተባብሮ ለመታገል ሲንቀሳቀስም ሆነ ለብቻው በአማራነቱ ለመደራጀት ሲፈልግ ዘረኛው ስርዓት ያለ የሌለ የአፈና ጉልበቱን በመጠቀም ዕንቁ የአማራ ልጆችን ሲገድል እና ሲያስር ብሎም በህጋዊ መንገድ የመሰረቱትን የፖለቲካ ድርጅት ሲነጥቅ እና ሲያፈርስ 27 ዓመት ሆኖታል፡፡ ይህ አይነት አካሄድ ከአሁን በኋላ በአማራ ላይ እንደማይሰራ ሊረዳ ያልቻለው ወያኔ መግቢያ ጉድጓዱን አርቆ በመቆፈር ላይ ይገኛል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ላይ የታሰሩ ሁሉም እስረኞች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን አድማ መምታትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ እርምጃ እንዲወስድ መዐሕድ ለመላው የአማራ ህዝብ ጥሪ የሚያስተላልፍ መሆኑን አበክሮ ያስጠነቅቃል፡፡

ድል ለአማራ ህዝብ!
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ)

Share this post