ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) የተሰጠ መግለጫ

 

ታህሳስ ፩፪ ፪ ሺ ፲ ዓ.ም.

ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) የተሰጠ መግለጫ (pdf)

ወቅታዊ “የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ምስረታ” ጥሪንና የአማራን ህዝብ ያገለለዉን ረቂቅ ሰነድ መዐሕድ ይቃወማል!

በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ መላው የአማራ ሕዝብን አግላይ የሆነው “የሽግግር ሰነድ” አማራውን ለሌላ ዙር እልቂት የሚዳርግ ነው!

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ቀውስና ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና የህዝቡ ተቃውሞ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ዲማ ነገዎ የሚመራዉ “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” የሽግግር መንግስት ረቂቅ ሰነድ አውጥቶ የምስረታ ጥሪን ለማቅረብ እየተሰናዳ መሆኑን በአንዳንድ መገናኛ አውታሮች ተላልፏል። “የሽግግር መንግስት ሰነዱ” ሙሉ በሙሉ ያገለለው ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጣው የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ሰነዱን በጽኑ ያወግዛል፤ በመላው አማራ ሕዝብ ላይ የተቀነባበረ የድምጽ አፈና እንደሆነም ያምናል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በአማራና ኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ለውጥ ፍላጎት ግለቱ ጨምሮ ከፍተኛ የትግል እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት አጋዚ ሠራዊት በርካታ የአማራና ኦሮሞ ተማሪዎች ተገድለዋል፤ ቆስለዉም ሆስፒታል ውስጥ፤ እዲሁም እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ብዙዎች መሆናቸውም ይታወቃል። “በአማራ ክልል” ትምህርት በተቋረጠባቸው ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት አልተጀመረም። በደብረ ማርቆስ ፣ደብረ ታቦር፣ ባህር ዳርና ወልድያ ዩኒቨርስቲዎች አብዛኛው ተማሪ ወደየቤተሰቡ መሄዱ ታውቋል።

ይህ በጭቁን ህዝቦች እየተደረገ ያለውን የሞት ሽረት የህልውናና የነጻነት ትግል በአየር ላይ ለመጥለፍ ሌት ተቀን የሚሰሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ግን አልታጡም። በመሆኑም ራሱን “ግንቦት ፯” ብሎ የሚጠራ ድርጅት ለአማራ ህዝብ ቀና አመለካከት የሌላቸውንና በየመድረኩ የአማራን ህዝብ ሲያጠቁ የነበሩ ግለሰቦች ከሚመሯቸዉ ድርጅቶች ጋር በማበር “የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ረቂቅ ሰነድን” አዘጋጅቻለሁ ብሏል። በዚህ ሂደት ውስጥም ከሲሶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱን ህዝብ፤ ማለትም አማራውን፤ በግለሰቦች ለመወከል ተሞክሯል። የደርግ አገዛዝ ሊወድቅ አጥቢያ ት.ህ.ነ.ግ፣ ኤ.ህ.ነ.ግ እና ኦ.ነ.ግ ተመሳሳይ የሽግግር መንግስት ሰነድን አርቅቀው ነበር። በተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚዎች የረቀቁት እኒህ ሁለቱ “የሽግግር መንግስት ሰነዶች” የታላቁን የአማራ ህዝብ ያላሳተፉ ነበሩ። በሁለቱም አጋጣሚዎች የተሰጠው መልስ ደግሞ “አማራን ሊወክል የሚችል ድርጅት አጣን” የሚል ውሃ የማያነሳ ምክንያት ነበር። በሎንደን በረቀቀው የያኔው የሽግግር መንግስት ስምምነት አማራ ባለመወከሉ የአማራው ህዝብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር (የአማራ ክልል የተባለውን ጨምሮ) የአገር ባለቤትነቱን ተነጥቋል፤ በጅምላ ተገድሏል፤ በገፍ ተፈናቅሏል። አሁንም በተመሳሳይ መልኩ በረቀቀው “የሽግግር መንግስት ሰነድ” የሚቋቋም መንግስት የአማራን ህዝብ ለተጨማሪ አደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በመዐሕድ በኩል ፍጹም ተቀባይነት የለውም። በቆራጥነት የሚታገለው አካሄድም ነው።

በተጨማሪም “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” የሽግግር መንግስት ምስረታ ጥሪ ሲያደርግ የአገራዊ ጉባዔው ሰነድ ዝርዝር ይዘትና የሽግግር መንግስቱ የትግበራ ዕቅዶችን በመንደፍ ከአራት ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ሥራዉን እንደሚያገባድድ ገልጿል። መዐሕድ የአማራ ድርጅቶች ሂደቱን በመቃወም የጋራ አቋም እንዲይዙና የአገሪቱን ወቅታዊ ሂደት በመከታተል ለአማራ ህዝብ የሚበጅ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ያደርጋል።

በመጨረሻም በማሕበራዊ ሜድያ የሚናፈሰው “የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) የአገራዊ ንቅናቄውን እንዲቀላቀል ጥሪ ቀርቦለት ውድቅ አድርጎታል” የሚለው መሠረተ ቢስ ወሬ መሆኑን ድርጅቱ ያሳውቃል። መዐሕድ ህጋዊ የሆነ ጥሪ ከየትኛውም አካል አልቀረበለትም። ይልቁንስ “አማራ ወኪል ድርጅት ስለሌለው እኛው እንፈጥርለታለን” በሚል እብሪት የየራሳቸው የፖለቲካ መርሃ-ግብር ያላቸውን ድርጅቶች የመጨፍለቅ አስነዋሪ ሙከራ ነው የተደረገው። በዚህ ሂደት ላይ መዐሕድ ለአማራው ህዝብ ይበጃል ያለው ተለዋጭ ምክረ ሀሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከሂደቱ ራሱን ሊያገል ችሏል። በመሆኑም የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ምንም አይነት ህጋዊ ጥሪ ከየትኛውም አካል እንዳልደረሰውና፤ የነበረው ሂደት በአማራው ህዝብ ውስጥ የትሮጃን ፈረስ ሚናን ሊወጣ የሚችል ድርጅት ለመፍጠር እንደነበር ለመላው አማራ ህዝብና ለድርጅታችን አጋሮች ለማሳወቅ እንወዳለን። አሁን የረቀቀው “የሽግግር ሰነድም” በት.ህ.ነ.ግ፣ ኦ.ነ.ግ እና ኤ.ህ.ነ.ግ የረቀቀው ተቅጽላ እንጂ የተለየ ባለመሆኑ የመላው አማራ ህዝብ ትግሉን ከመቸውም ጊዜ በመረረ ሁኔታ አጠናክሮ እንዲቀጥል ስንል እናስገነዝባለን። የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ለአማራው ህዝብ ይበጃል የሚለውን ተለዋጭ ሰነድ አዘጋጅቶ የጨረሰ ሲሆን በቅርብም ለህዝባችን ይፋ ያደርጋል።

ከሰላምታ ጋር!
የአማራ ህዝብ ያሸንፋል!

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ)

Share this post