ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ መግለጫ

ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ መግለጫ (pdf)

ጥቅምት 23 2010 ዓ.ም

በመላው ኢትዮጵያ የዐማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሱ ጭፍጨፋዎችና መጠኑን ያለፈ የሰብዓዊ መብት ረገጣው ተባብሶ ቀጥሏል!

ፋሽስታዊ አገዛዙ አገር በቀልና ዓለማቀፍ የበጎ አድራጎት ማህበራት የእርዳታ እጆችን መከልከሉን በጥብቅ እናወግዛለን! በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያ፣ መፈናቀልና ወከባ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። በዚህ ወር ብቻ እንኳን አያሌ ወገኖቻችን በኢሉባቦር፣ በካማሽና ሸዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩም የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል፤ ቤት አልባም ሆነዋል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አካላት እርዳታ እንዳያገኙና የችግሩ ጥልቀት እንዳይታወቅ በሚል የየአካባቢው ባለሥልጣናት እልቂቱ የተካሄደባቸው ቦታዎች እንዳይጎበኙ በታጠቁ ሃይሎች እያስጠበቁ ናቸው። የፋሽስታዊ አገዛዙና ግብረ አበሮቹ እኩይ ተግባር በዚህ የሚያበቃ አይደለም። ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት የተባለ ማህበር ለተጎጂ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ይሆን ዘንድ የላከው የ$25,000 (ሃያ አምስት ሺህ) ዶላር እርዳታ ለተጎጅዎች እንዳይደርስ መደረጉን የተለያዩ የብዙሃን መገናኛ አውታሮች ዘግበውታል። የኢሉባቦር ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከፈተው ደብተርም በአገዛዙ ደህንነቶች ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ ሆኗል።

የዐማራ ሕዝብ፦

1ኛ) እንደሕዝብ መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጆች የመኖር መብት የተነጠቀ ስለሆነ፤

2ኛ) በኢትዮጵያ ምድር ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት ንብረት የማፍራት መብቱን የተነጠቀ ስለሆነ፤

3ኛ) በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋና ሰብዓዊ ቀውስ ወቅት ተገቢውን እርዳታ የማግኘት መብቱን ሙሉ በሙሉ የተነጠቀ ስለሆነ፤

4ኛ) በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዐማራውን መግደል ወይም አካላዊ ጉዳት ማድረስ በሕግ የማይጠየቅበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ፤

5ኛ) በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወክለውና መብትና ጥቅሙን የሚያስከብርለት ድርጅታዊ ውክልና የሌለው ስለሆነ እና

6ኛ) ከምንግዜውም በላይ ሕልውናው አደጋ ላይ በመሆኑ፤

የመላው ዐማራ ሕዝብ ከጫፍ እስከጫፍ ተነስቶ ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል የተጋረጡበት አደጋዎች እንዲመክት የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ጥሪውን ያቀርባል። እየደረሰበት ያለው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጥቃቶች በተደራጁ ኃይሎች በመሆኑና ይህንንም መመከት የሚቻለው በተደራጀ መልኩ ስለሆነ መላው ዐማራ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን እንዲቀላቀል ስንል በአክብሮት ጥሪያችን እናቀርባለን። የዐማራ ሕዝብ ጠላቶቹን ማሸነፍ የሚችለው ከአብራኩ የወጡ ቆራጥ ልጆቹ ተደራጅተው በሚያደርጉት ትግል ብቻ ነው!

ዐማራ ያሸንፋል!
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት

Share this post